በሙስሐፉ ውስጥ 81ኛው ሱራ ነው፤ 29 አንቀጾች አሉት፤ በገጽ 586 ይጀምራል።
بِسۡمِ ٱللَّهِ ٱلرَّحۡمَٰنِ ٱلرَّحِيمِ
1. ጸሐይ በተጠቀለለች ጊዜ፤
2. ከዋክብትም በረገፉ ጊዜ፤
3. ተራራዎች ከቦታቸው በተነዱ ጊዜ፤
4. የአስር ወር እርጉዝ ግመሎች ያለጠባቂ በተተው ጊዜ፤
5. አራዊቶችም በተሰበሰቡ ጊዜ፤
6. ባህሮችም በተቀጣጠሉ ጊዜ፤
7. ነፍሶች በተቆራኙ ጊዜ፤
8. ከነሕይወቷ የተቀበረችው ሴት ልጅም በተጠየቀች ጊዜ፤
9. በምን ወንጀል እንደተገደለች፤ በተጠየቀች ጊዜ፤
10. ጹሑፎችም በተዘረጉ ጊዜ፤
11. ሰማይም በተገሸለጠች ጊዜ፤
12. ገሀነምም በተነደደች ጊዜ፤
13. ገነትም በተቀረበች ጊዜ፤
14. ነፍስ (ሁሉ ከስራ) ያቀረበችውን ታውቃለች፤
15. (ሁኔታው ከሓዲያን እንደሚሉት አይደለም)። ተመላሾች በሆኑት (ከዋክብት) እምላለሁ።
16. አንዳንድ ጊዜ ሂያጆች በሌላ ጊዜ ገቢዎች በሆኑት
17. በሌሊቱም (ጨለማውን) በጠነሰሰ ጊዜ፤
18. በንጋትም (በብርሃን) በተነፈሰ ጊዜ እምላለሁ።
19. እርሱ (ቁርኣን) የተከበረው መልዕክተኛ (ጅብሪል) ቃል ነው።
20. የኃይል ባለቤት የሆነ፤ ከዐርሹ ባለቤት ዘንድም ባለሟል የሆነ፤
21. በዚያ ስፍራ ትዕዛዙ ተሰሚ፤ ታማኝም የሆነው (መልዕክተኛ ቃል ነው)።
22. ባልደረባችሁም (ሙሐመድ) እብድ አይደለም።
23. (ጅብሪልን) በግልጹ አድማስ ላይ በእርግጥ አይቶታል።
24. እርሱም በሩቁ ወሬ ላይ ሰሳች (ንፉግ) አይደለም።
25. (ቁርኣን) የርጉም ሰይጣን ቃልም አይደለም።
26. ታዲያ (ይህንን በተመለከተ) ወዴት ትሄዳላችሁ?
27. እርሱ የዓለማት መገሰጫ እንጂ ሌላ አይደለም።
28. ከናንተ መካከል ቀጥተኛ መሆንን ለፈለገ (ሁሉ መገሰጫ) ነው።
29. (ሰዎች ሆይ!) የዓለማት ጌታ የሆነው አላህ ካልሻ በስተቀር እናንተ አንድም ነገር አትሹም።
የቁርኣን ፍቺ ትርጉም፦ Amharic Translation - Africa Academy፣ እትም 1.0.3፤ ከQuranEnc.com ያለ ምንም ለውጥ የቀረበ። (QuranEnc.com)
ትርጉም የቁርኣንን ፍቺዎች ያስተላልፋል እንጂ ራሱ ቁርኣን አይደለም፤ ቁርኣን ከላይ ያለው የዐረብኛ ጽሑፍ ነው።